ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ፖሊስ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐሰተኛ መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳሰበ።
ፖሊስ ባስተላለፈው መልዕክት÷ የአዲስ አበባ ሰላም መሆን እንቅልፍ የነሳቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ሕብረተሰቡን ሥጋት ላይ ለመጣል እየጣሩ መሆኑን አመላክቷል፡፡
እነዚህ አካላት በተደጋጋሚ በአዲስ አበባ ሰላም እንደሌለና ሕዝቡ ሥጋት ውስጥ እንወደቀ ለማስመሰል በበሬ ወለደ ዲስኩራቸው ተጠምደው ቢጮሁም÷ ሰላም ወዳዱ የመዲናዋ ነዋሪ ለሐሰተኛ ትርክታቸው ጆሮ ሳይሰጥ ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር የአካባቢውን ሰላም እየጠበቀ እንደሚገኝም ነው የገለጸው፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሰላምን ለማደፍረስ የሄዱበት ርቀት አልሳካ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች አሁን ላይ ስልታቸውን ቀይረው በማኅበራዊ ሚዲያ ፈፅሞ ያልተፈጠረን ነገር የሆነ በማስመሰል ሕዝብን ለማደናገር እየሞከሩ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
በዚህም ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ ጥቃት ለመፈፅም በኅቡዕ የተደራጀ ቡድን እንዳለ በማስመሰል ሳር ቤት አካባቢ አውቶቡስ ላይ ቦንብ ማፈንዳቱን የሚገልፅ የፈጠራ ወሬ እያሰራጩ ነው ብሏል ፖሊስ፡፡
በመሆኑም ይህ ከእውነታ የራቀ በአዲስ አበባ ሰላም የለም ለማስባል ሆን ተብሎ የተሰራጨ የሐሰት መረጃ መሆኑን ሁሉም የከተማችን ነዋሪዎች ሊገነዘቡ ይገባል ነው ያለው፡፡
እነዚህ የከተማችንን ሰላም የማይፈልጉ አካላት የሌት ተቀን ህልማቸውን ቲክ ቶክ በተሰኘ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየገለፁ ነው ያለው ፖሊስ÷ በአዲስ አበባ ያለው ሰላም አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ፖሊስ ከመቼውም ጊዜ በላይ የፀጥታ ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝ አረጋግጧል፡፡
ሕብረተሰቡም ትክክለኛ መረጃዎችን ከትክክለኛው ቦታ የማግኘት ባህሉን ሊያዳብር እንደሚገባ በማሳሰብ÷ ሐሰተኛ መረጃን በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያሰራጩ አካላት ላይ በሕግ አግባብ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡