Fana: At a Speed of Life!

ማህበሩን ከ12 ሚሊየን ብር በላይ ያሳጡ ግለሰቦች እስከ 18 ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በህብረት ስራ ማህበራት ስም ሀሰተኛ የገቢ ደረሰኝ በማዘጋጀትና ገቢ በመሰብሰብ እንዲሁም የህብረት ስራ ማህበሩን የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን ለግል ጥቅም በማዋል በአጠቃላይ ከ12 ሚሊየን ብር በላይ አሳጥተዋል የተባሉ ሶስት ተከሳሾች በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የቤኪምቲ የገበሬ ህብረት ስራ ማህበር ሰራተኛ የነበሩት ታምሩ ፋጂ፣ ጎበና ጫሊሳ እና ኦሮሚያ አጃባ ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ ምዕራብ ሸዋ ዞን ምድብ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የሙስና ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን ድንጋጌን ተላልፈዋል በማለት ባቀረበባቸው ክስ 1ኛ ተከሳሽ ታምሩ ፋጂ የተባለው ግለሰብ በህብረት ስራ ማህበሩ ውስጥ ገንዘብ ያዥ ሆኖ ሲሰራ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ 10 ሚሊየን 482 ሺህ 131 ብር ከ15 ሳንቲም የሆነ ገንዘብ ማጉደሉ ተጠቅሷል፡፡

ጎበና ጫሊሳ የተባለው ተከሳሽ ደግሞ የህብረት ስራ ማህበሩ መጋዘን ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ 42 ኩንታል ማዳበሪያ፣ አምስት ኩንታል በቆሎ፣ 125 ኩንታል ነጭ ሽንኩርትና ሌሎች ምርቶችን ባጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 2 ሚሊየን 441 ሺህ 34 ብር ከ34 ሳንቲም የሆኑ ምርቶችን ለግል ጥቅሙ እንዲውል አድርጓል በማለት በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል።

በሌላኛው ክስ ደግሞ ኦሮሚያ አጃባ የተባለው ተከሳሽ ከሌሎቹ ተከሳሾች ጋር በመሆን በማህበሩ ስም ስምንት ሀሰተኛ የገቢ ደረሰኞችን በማሳተምና በመጠቀም 305 ሺህ 287 ብር ከ56 ሳንቲም ገቢ በሀሰተኛ ደረሰኝ በመሰብሰብ ለግል ጥቅም እንዲውል ማድረጉ ተጠቅሶ ባሳለፍነው ዓመት ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ተመላክቷል።

ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ከደረሳቸው በኋላ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ አስረጂና ገላጭ የሰነድ ማስረጃና የሰው ምስክሮችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ቢሰጥም ተከሳሾቹ በተገቢው መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ከዚም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመያዝ ታምሩ ፋጂ የተባለው ተከሳሽን በ18 ዓመት ፅኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

ኦሮሚያ አጃባ የተባለውን ተከሳሽ ደግሞ በ12 ዓመት ፅኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ጎበና ጫሊሳ የተባለው ተከሳሽን ደግሞ በ5 ዓመት ፅኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።

በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ የተከሳሾቹ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች እግድ ተጥሎ እንዲወረስ ማመልከቻ ማቅረቡን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የንብረት ግምቱ በባለሙያ ተጠንቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.