የ’ንኢሌ ፓልም ስፕሪንግ ሎጅ’ ግንባታ ሒደት እየተፋጠነ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል በገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር እየተገነባ የሚገኘው የ’ንኢሌ ፓልም ስፕሪንግ ሎጅ’ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ተናገሩ።
የንኢሌ ፓልም ስፕሪንግ ሎጅ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት በክልሉ አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ዶሆ ቀበሌ ነው እየተገነባ የሚገኘው።
በሥፍራው ተገኝተው ሥራውን የተመለከቱት አምባሳደር ናሲሴ ”የሎጁ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው፤ የግንባታ ሒደቱም 24 በመቶ ደርሷል” ብለዋል።
እስካሁንም በሎጁ ሰው ሰራሽ ሐይቆችና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መገንባታቸውን ጠቁመው፤ የሎጁ ግንባታ አሁን በተያዘው ፍጥነት ከቀጠለ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ይበቃል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት በሎጁ የሚካሄዱትን የመሠረተ ልማት ግንባታ በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥልም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሎጁን የመሠረት ድንጋይ ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡