ተቋሙ ቅሬታዎችን በማጣራት የሚያቀርበው ምክረ ሀሳብ ትኩረት እንዲሰጠው ጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በተለያየ መንገድ የሚደርሱትን ቅሬታዎች በማጣራት የሚያቀርበውን ምክረ ሀሳብ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ጠየቀ።
ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በምርመራና በመፍትሔ ሃሳብ አፈፃፀሞች ዙሪያ ከፌዴራልና ከክልል የፍትህ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ የውይይት አካሂዷል።
በኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ እንዳለ ሀይሌ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደተናገሩት÷ የዜጎች መብትና ነፃነት በአግባቡ ከተከበረ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ ጠቀሜታ አለው።
ተቋሙም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡለትን ቅሬታዎች ተቀብሎ በመመርመር የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል ብለዋል።
መብትን በማስከበር ሂደት የሚያገጥሙ ተግዳሮቶችን ለይቶ መፍታት የሁሉም አካላት ድርሻ መሆኑን የጋራ ግንዛቤ መያዝ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምም የመንግስትም ሆኑ የግል ተቋማት በዜጎች ላይ የአስተዳደር በደል እንዳይፈፅሙ አስቀድሞ ለመከላከል፣ ተፈፅሞ ሲገኝም በአፋጣኝ እንዲታረም የማድረግ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዚህ ሂደትም ተቋሙ በተለያየ መንገድ የሚደርሱትን ቅሬታዎች በማጣራት የሚያቀርበውን ምክረ ሀሳብ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በበኩላቸው÷ ዜጎች ከህግና ፍትህ ስርዓቱ ተጠቃሚ መሆናቸው በየደረጃው ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ በዘርፉ እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ጠቋሚ ነው ብለዋል።