Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአህጉር ደረጃ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲረጋገጥ እየሰራች እንደሆነ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በብሔራዊና አህጉር ደረጃ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲረጋገጥ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዓለም የውሃ ቀን “ውሃ ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ማሙሻ ሃይሉ በወቅቱ እንዳሉት፤ ውሃን በእኩልነትና በፍትሃዊነት መጠቀም ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአህጉር እና በብሔራዊ ደረጃ ፍትሃዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ በአህጉር ደረጃ በእኩልነትና ፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ የውሃ ሃብት አጠቃቀም እንዲኖር ጉልህ ሚና መጫወቷን አንስተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን ገልጸው፤ በዚህም ሃብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ እያዋሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ የውሃ ሃብት አጠቃቀምን በአግባቡ ለማስተዳደር የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር መቅረጹንም እንደተናገሩ ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲረጋገጥ በማድረግ ውሃ የሰላምና አብሮ የማደግ ምንጭ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ የውሃ ሃብት አጠቃቀምና በጋራ የመልማት ጽኑ አቋሟን አሁንም እንደቀጠለች የገለጹት ደግሞ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው ናቸው።

የዓለም አቀፉ የውሃ አስተዳደር ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ዶክተር አብዱልካሪም ሰኢድ፤ በአፍሪካ ለውሃ ሃብት መረጃ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የውሃ ሃብትን በፍትሃዊነትና እኩልነት ለመጠቀም፣ የሴቶች ድርሻ በውሃ ዲፕሎማሲ፣ የውሃ ሃብት መረጃና የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ላይ ትኩረት ያደረጉ ጹህፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.