ሚኒስትሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ በሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት የተዋቀረውን የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ከፍተኛ ውይይት ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አምባሳደር ታዬ በሱዳን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ለተዋቀረው የሱዳን ፓናል ኢትዮጵያ ደስተኛ መሆኗንና የምትችለውን ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።
አምባሳደር ታዬ በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት ሱዳናያውን በባለቤትነት የተሳተፉበት እና በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ሁሉን አቀፍና አካታች ውይይት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በተለይም በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር የሚከናወኑ የሰላም አማራጮችን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።
የተዋቀረው ቡድን ሊቀመንበር ሙሀመድ ኢብን ቻምባስ በበኩላቸው፤ በግጭቱ ምክንያት ለተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስና ተያያዥ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ሙሀመድ ኢብን ቻምባስ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ከፍተኛ ፓናል በህብረቱ የተኩስ ድምፅ ማጥፋት ልዩ ልዑክ በሆኑት መሐመድ ቻምባስ የሚመራ ሲሆን፤ የኡጋንዳ የቀድሞ ም/ፕሬዚዳንት ሰፔሊኦዛ ካዚኮዌ (ዶ/ር) እንዲሁም የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ልዩ ተወካይ አምባሳደር ፍራሲስኮ ማድራን በአባልነት ያቀፈ መሆኑ ተጠቁሟል።