በሶማሌ ክልል በመስኖ የሩዝ ሰብል የማልማት ንቅናቄ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በመስኖ የሩዝ ሰብል የማልማት ንቅናቄ በሸበሌ ዞን ምዕራብ ጎዴ መስኖ ፕሮጀክት በቤርአኖ በይፋ ተጀምሯል።
ንቅናቄውን የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ እና የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አስጀምረዋል።
በዚህ ወቅትም በአንድ ሄክታር 45 ኩንታል ምርት በመሰብሰብ በመስኖ ከሚለማው ከ2 ሺህ ሄክታር 90 ሺህ ኩንታል የሩዝ ምርት ለመሠብሰብ መታቀዱ ተመላክቷል፡፡
በቀጣይ 3 ዓመታት በመስኖ አማካኝነት 10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሩዝ ሰብል በማልማት 500 ሺህ ኩንታል ምርት የመሰብሰብ ዕቅድ መኖሩ ተጠቁሟል።
አቶ ሙስጠፌ÷ የሩዝ መስኖ ልማቱ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለመቀነስ፣ ገቢ ምርትን ለመተካት እና በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ አሁንም በስፋት የመልማት ዕምቅ አቅም እንዳለ ጠቁመው÷ መሰል ሰፋፊ የመስኖ ልማት ሥራዎች መከናወናቸው ለክልሉ የግብርና ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ባለፉት ዓመታት በተከናወነ ሥራ 50 በመቶ ከውጭ የሚገባ ሩዝ ምርትን ሀገር ውስጥ በማምረት መተካት ተችሏል ብለዋል፡፡