Fana: At a Speed of Life!

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የድርሻውን እንደሚወጣ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ምሁራን የራሳቸውን አስተዋፅዖ ሊያደርጉ እንደሚገባ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሀሰን የሱፍ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

በባህር በር ዙሪያ በየደረጃው የሚደረጉ ውይይቶች የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ የሚያግዙ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ አመራርና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ”የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ፣ ለኢኮኖሚ፣ ታሪክና ህጋዊ አግባብ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት አካሄዷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሀሰን የሱፍ (ዶ/ር) በመድረኩ÷ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በመሆኑ ይደገፋል ብለዋል።

ጥያቄው የሀገሪቷን ልማትና እድገት ለማረጋገጥ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ይህ ጉዳይ የሀገራችን እና ትውልዱ ተስፋ ስለሆነ አስፈላጊነቱን በማስገንዘብ ረገድ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተለይም ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በባህር በር ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ደምስ ፈረዲሳ (ዶ/ር) ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ፤ የባህር በር የአንድን ሀገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲ አቅም የሚያጎለብት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ኢኮሚያዋን የበለጠ ለማጠናከርና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ጥያቄውን ማንሳቷ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።

የባህር በር ጥያቄው ውጤት እንዲያመጣ መንግስት ከሚያደርግው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ምሁራንም ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ በጥናትና ምርምር ማገዝ አለባቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.