Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባን የትስስርና ብሔራዊ ትርክት የተረጋገጠባት ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባን የትስስር እና ብሔራዊ ትርክት የበላይነት የተረጋገጠባት ከተማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የአባላት ኮንፈረንስ “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና “በሚል መሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው፡፡

በኮንፈረንሱ የተገኙት አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት ÷ የብልጽግና ፓርቲ በግማሽ ምርጫ ዘመን አፈጻጸሙ በተለያዩ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በተለይም በግብርና፣ በአረጓዴ አሻራ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን ፣በአይሲቲ፣ በቱሪዝመና ሌሎች ዘርፎች ላይ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን አስረድተዋል፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍ በተከናወነ ሥራም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከአንድ እስከ አምስት ከፍተኛ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂ ዲፒ) ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

በወንድማማችነት እሴት ላይ የቆመ ህብረ ብሔራዊ አንድነት መገንባት እና ብዝሃ ልሳን የሆነ የፖለቲካ ማህበረሰብ መገንባት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ብልጽግና ማሳያ ለማድረግ በትኩረት እና በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አቶ አደም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም መዲናዋ የትስስር ትርክት፣ አካታችነት ፣ አቃፊነት፣ ፍትሃዊነት፣ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እና ወንድማማችነት የሰፈነባት ከተማ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭት፣ ዝቅተኛ የሀገር ውስጥ የቁጠባ ባህልና ኢንቨስትመንት፣ የበጀት ጉድለት እና ዕዳ ተጋላጭነቶች የተስተዋሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የፓርቲው አመራሮችና አባላት የዓለምና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት በአንድነትና በትብብር ተግዳሮቶቹን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ለሕዝብ አንገብጋቢየሆኑ ጥያቄዎችን መፍትሔ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው ÷ በተለይም የሰላም፣ የዋጋ ንረትን መቀነስ ፣ የሥራ እድል መፍጠርና እና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ላይ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡

ፓርቲው ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አንጻር በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን በተጀመረው አማራጭ በሰላማዊ አካሄድ መፍትሔ እንዲያገኙ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ገበያን ማዘመን፣ እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴን ማሳለጥ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.