በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለሕግ በማቅረብ ጠንካራ አፈፃፀም መመዝገቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕገወጥ የሕፃናት ዝውውርን በመከታተልና ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለሕግ በማቅረብ ጠንካራ አፈፃፀም መመዝገቡን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከሕዝብና ከመንግሥት የተጣለበትን ተልዕኮ ለመወጣት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ አበረታች ውጤት እያመጣ መሆኑ ገልጿል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያለፉት ስድስት ወራት ስራ አፈጻጸምና የቀጣይ ስድስት ወራት የተከለሰ እቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት እያካሄደ ነው።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው በመድረኩ እንደገለጹት÷ ኮሚሽኑ ለሕዝቡ የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ዘርግቷል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የአስተዳደር ልማት ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር እንዳለ አበራ በበኩላቸው÷ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በወንጀል መከላከል ተግባር አበረታች ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።
በተለይም የሕገወጥ መሳሪያ ዝውውርን በመከላከል ረገድ ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል።
በተጨማም÷ የኮንትሮባንድ ንግድን በመቆጣጠር፣ ሕገወጥ የሕፃናት ዝውውርን በመከታተል እንዲሁም ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለሕግ በማቅረብ ጠንካራ አፈፃፀም እንዳለ በሪፖርቱ ገልፀዋል።
በትራፊክ ደህንነት ስራ ዘርፍ በክልሉ በሚገኙ ሦስት ዞኖች ላይ የትራፊክ አደጋ አስጊ ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ለመቆጣጠር በዘመቻ መልክ የቁጥጥርና የክትትል ስራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
በማህሌት ኡኩሞ እና መለሰ ታደለ