አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በ148ኛው የዓለም ፓርላማዎች ኅብረት ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ በጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 148ኛው የዓለም ፓርላማዎች ኅብረት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡
ጉባዔው “የፓርላማ ዲፕሎማሲ፤ ለሰላምና መግባባት ድልድይ መገንባት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ሲሆን እስከ ፈረንጆቹ መጋቢት 27 ቀን 2024 ድረስ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ባደረጉት ንግግርም÷ በዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችሉ ሐሳቦች ላይ የፓርላማ አባላት የተሻለ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ጉባዔው የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚበረክት አመላክተዋል፡፡
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚካሄዱ ግጭቶችና ጦርነቶችን ለማስቆም ከፖለቲካዊ ቁርጠኝነት በተጨማሪ የፓርላማ አባላት ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታን ለማምጣት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን አስረድተው÷ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰውን ግጭት ለማስቆም የተደረሰውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር መንግስት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ቀጣናውን በኢኮኖሚ ማስተሳሰር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው÷ ኢትዮጵያ በቀጣናው ይህንን ለመፍጠር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ወሳኝ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗን አብራርተዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር መድረክ ማመቻቸትን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተቱ በርካታ ውይይቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ “የፓርላማ ዲፕሎማሲ፤ ለሰላምና መግባባት ድልድይ መገንባት” የሚለው ዓላማ የተሳካ እንዲሆን ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን ከፌደሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ሩሲያ ባዘጋጀችው በብሪክስ አባል ሀገራት አፈ-ጉባዔዎች መድረክ ላይ ተሳትፈው ባደረጉት ንግግርም÷ የአባል ሀገራት የፓርላማ ኅብረት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ የበኩሏን ተሳትፎ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።