በመዲናዋ እየተከሰተ ላለው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሕብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የኤሌክትሪክ መስመር የማዛወር ሥራ ምክንያት የሚፈጠርን የአገልግሎት መቆራረጥ ሕብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጠየቀ፡፡
በመዲናዋ እየተከናወነ በሚገኘው የመንገድ ኮርደር ፕሮጀክትና ተያያዥ የልማት ሥራዎች ምክንያት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የከፍተኛና የዝቅተኛ የኤሌክትሪክ መስመር የማዛወር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሥራው ሲከናወን ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ እንዲሁም አደጋ እንዳይከሰት ሲባልም ሥራው በሚከናወንባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ ወይም አልፎ አልፎ ለተወሰኑ ሰዓታት እየተቋረጠ እንደሚገኝ አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
የመስመር ማዛወር ሥራዎችን በጥንቃቄና በፍጥነት በማከናወን አገልግሎቱን ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ደንበኞችም ጉዳዩን ተረድተው በትዕግስት እንዲጠብቁ ያስገነዘበው አገልግሎቱ ፥ ለሚፈጠሩ የአገልግሎት መስተጓጎሎች ይቅርታ ጠይቋል፡፡