Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት መደበኛ ጉባኤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 43ኛው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት መደበኛ ጉባኤ “ጠንካራ የተማሪዎች አደረጃጀት ለተሻለች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የመሰረተ ልማትና አስተዳደር ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር)÷የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ሂደት የበኩላቸውን ሚና መወጣት የሚችሉ ምሩቃንን ለማፍራት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያደርጉት ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የተማሪዎች ህብረት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተሳትፎው እንዲያድግና ውጤታማ እንዲሆን ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

ህብረቱ የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታ የተመቸ እንዲሆን ፣የተማሪዎች መብት እንዲጠበቅና ግዴታቸውንም እንዲወጡ ከሚኒስቴሩና ከዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን የትምህርት ሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሚኒስቴሩ የአስተዳደር ጉዳዮች ዴስክ ሀላፊ አቶ አብዶ ናስር በበኩላቸው÷ አዲስ የተመረጡ የህብረቱ አመራሮች በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ሀገርን ያስቀደመ ህብረብሄራዊ አንድነት፣ መቻቻልና ፍቅር እንዲጎለብት መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የሀገር አቀፍ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ሚካኤል ያቦነሽ÷ የህብረቱ አመራሮች በተቋማት ውስጥ የሰሯቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውን በመግለጽ ተማሪዎችም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖችን በመርዳት አለኝታቸውን እንዲገልጹ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.