የፋይናንስ ተቋማት አካታችና ደኅንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ፋይንስ አገልግሎት ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አካታችና ደኅንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ፋይንስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን የፋይናንስ ተቋማት ገለጹ።
የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች÷ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማካተት ረገድ ያለውን የፋይናንስ ዘርፍ ክፍተት ለመድፈን አስቻይ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ባንክ ፐሬዚዳንት ተፈሪ መለስ÷ ባንካቸው አካታች የሆነ የፋይናንስ ስርዓትን ለማረጋገጥ የራሱን ተቋማዊ ፖሊሲ ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የእናት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ትዕግስት አባተ በበኩላቸው÷ ባንካችው ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ በተለይም ለሴቶች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የእናት ባንክ አመራሮች 60 በመቶው ሴቶች እንደሆኑ ገልጸው÷ ይህም እንደ ሀገር በፋይናንስ ዘርፍ እምርታ ውስጥ የራሱን ሚና እያበረከተ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
የፋይናንስ ተቋማቱ የሴቶችን አካታችነት ከማረጋገጥ ባሻገር ደኅንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ መሳይ ኢንሴኔ እንዳሉት÷ ተቋሙ ሴቶችና ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ነው።
ባለፉት ስድስት ወራት በነበራቸው አፈጻጸም የሴቶች ድርሻ 46 በመቶ እንደነበር በመግለጽ በቀጣይ የሴቶችን ድርሻ 50 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል።
የከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ ታመነ በበኩላቸው÷ እንደ ፋይናንስ ተቋም አካታችነቱ የተጠበቀ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።