በመዲናዋ የኮሪደር ልማት ቅርሶችን የመንከባከብና የመጠገን ስራ እየተከናወነ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የመልሶ ግንባታና ኮሪደር ልማት የሀገር ሃብትና ቅርሶችን የመጠበቅ የመንከባከብና የመጠገን ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ሃብትና ቅርሶች በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በመጠገን ለትውልድ እንዲተላለፉ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።
አዲስ አበባን ጨምሮ የቅርስ ጥበቃና መስህቦችን የማስፋት ስራ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የመጠገን ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በመዲናዋ የአራዳ፣ ጉለሌ፣ ቂርቆስ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የአዲስ አበባ ቀደምት የምስረታ አካል በመሆናቸው የኪነ-ሕንፃና መልክዓ ከተማነትን የሚያሳዩ መታሰቢያዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም በመዲናዋ የቅርስ መስፈርቶችን ሳያሟሉ የተመዘገቡ መኖራቸውን አስታውሰው፤ ዓለም አቀፍ የቅርስ ምዝገባ ተሞክሮን መነሻ በማድረግ በተዘጋጀ መመሪያ መሰረት በአዲስ መልክ የቅርስ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚሁ መሰረት ከዚህ በፊት የተመዘገቡ በቅርስነት የሚቀጥሉ ሲኖሩ በመመሪያው መሰረት መስፈርቱን የማያሟሉ ደግሞ አይቀጥሉም ብለዋል።
በመሆኑም በአዲስ አበባ የመልሶ ግንባታና ኮሪደር ልማት መጠበቅ ያለባቸው ቅርሶች እንዲጠበቁ እየተደረገ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ከማህበራዊ ትውስታ፣ ዘመናዊነትና መዝናኛነት ጋር በተገናኘ የቆዩ ቤቶች ሁሉ ቅርስ ሊሆኑ አይችሉም ሲሉም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም መርካቶ የቃኘው ሻለቃ ሆቴል፣ ቤላ የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ቤትና ፒያሳ የአድዋ ሆቴል የቅርስነት መስፈርት ሳያሟሉ ተመዝግበው እንደነበርም አስታውሰዋል።
በመሆኑም በመልሶ ግንባታና ኮሪደር ልማት ቅርሶች ተለይተው በቅርስ ምዝገባ መስፈርት ተመዝግበው እንዲጠበቁ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በየትኛውም ዓለም ልማትና ቅርስ ጥበቃ ሚዛኑን ጠብቆ እንደሚጓዝ ጠቁመው፤ ቅርስ ጥበቃና ልማትን ማጣጣም ግዴታ ነው ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አስረድተዋል።
በመሆኑም የቅርስ ጥበቃና የልማት ስራዎች ተመጋግበው እንዲሄዱ በማድረግ የቅርስ መስፈርት የማያሟሉ ቤቶችንና አካባቢዎችን በመልሶ ልማት የቀደመ ስያሜና አገልግሎታቸው እንዲቀጥል ይደረጋል ነው ያሉት።