ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮ-ቴሌኮምን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መጋት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ የኢትዮ ቴሌኮም የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሰየሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከቦርዱ አባላት ጋር ኢትዮ-ቴሌኮምን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በዓድዋ የድል መታሰቢያ የሚገኘውን ኤክስፒሪየንስ ማዕከል፣ የፕሪሚየም አገልግሎት ማዕከል፣ ሞጁላር ዳታ ሴንተር እና የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ኩባንያው የኮኔክቲቪቲ ተደራሽነት እና ጥራት ከማሻሻል ባሻገር የዲጂታል ሶሉሽኖችን እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ የሕዝብን ሕይወት ለማቅለል በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በቴሌኮም እና በዲጂታል መሠረተ ልማት አቅም የተፈጠረውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም የመንግስት ተቋማት አሰራሮቻቸውን በዲጂታል በማዘመን ፈጣን፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት ማቅረብ እንዲችሉ የተገነቡ የዲጂታል አቅሞችን እንዲያውቁት እና እንዲጠቀሙበት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቷል፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ዕውን ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረትና አስተዋጽኦ በማድነቅ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቦርዱ ተገቢውን ድጋፍ እና አመራር እንደሚሰጥ መነሳቱንም የኩባንያው መረጃ ያመላክታል።