የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላም በአዲስ አበባ የተጀመረው የልማት ኮሪደር ዓላማ እና አሁን ያለበት ደረጃ ለተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮቹ ማብራሪያ ተሰጥቷል::
ጎብኚዎቹ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለቀጣይ ትውልድ ቋሚ ቅርስ በሚሆን መልኩ መገንባቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጋራ ታሪካችንን በልኩ ሰንዶ የያዘና አንድነታችንን የሚያጸና ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ያሉት ተወካዮቹ÷የልማት ኮሪደሩ ዓላማም ከተማዋን ማስዋብ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ከልማት ተነሺዎች የሚነሳ ማንኛውንም ቅሬታ ከፍተኛ አመራሩ አዳምጦ ምላሽ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውንም የከንቲባ ጽ/ ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገዢው ፓርቲ የሰራቸውን የልማት ሥራዎች በማየት ማመስገን እና እውነታውን መመስከር በፖለቲካ ስርዓታችን ውስጥ አዲስ ባህል በመሆኑ ሊዳብር ይገባል ብለዋል፡፡