ዓለምአቀፋዊ ዜና

ፖፕ ፍራንሲስ በጋዛ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

By Meseret Awoke

March 31, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ በትንሳኤ በዓል በጋዛ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፖፕ ፍራንሲስ የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሰላም ላይ ትኩረት ያደረገ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግና ሁሉም የእስራኤል ታጋቾች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

የ87 ዓመቱ የሮማ ካቶሊክ ጳጳስ በጋዛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግም በአጽንኦት ጠይቀዋል፡፡

በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ እስካሁን ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች ለህልፈት ሲዳረጉ ፥ ለአካል ጉዳት የተጋለጡ ዜጎች ቁጥርም ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በሌላ በኩል በጋዛና አካባቢው የሚገኙ ዜጎች ለአስከፊ ረሃብ አደጋ እንደተጋለጡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መግለጻቸውንም ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡