Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ ከግብርና ግብዓት ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ራሱን እንዲከላከል ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ ከምርጥ ዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓት ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ራሱን ሊከላከል እንደሚገባ የአማራ ክልል የግብርና ጥራትና ደህንነት ባለስልጣን መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሞላ ካሳ እንዳሉት፥ ለገበያ የሚሆን ዘር በማምረት እና በማከፋፈል ተግባር ላይ የሚሰማራ ማንኛውም አካል የዘር ማምረት፣ ማከፋፈል እና መቸርቸር የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መያዝ አለበት፡፡

የኢትዮጵያ የዘር ደረጃ መስፈርቶችን ያላሟላ ዘር ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ክልክል መሆኑን ጠቅሰው፤ የመለያ ምልክት ወይም ሌላ ህጋዊ ሰነድ የለወጠ በወንጀል እንደሚጠየቅ አስገንዝበዋል።

በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚፈልጉ አካላት ዘር ለማምረት፤ ለማከፋፈልና ለመቸርቸር ምንም ዓይነት የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሳይኖራቸው ጥራቱን ያልጠበቀና ምንጩ ያልታወቀ ዘር ለማቅረብ ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም ዘር በማስመሰል፣ የተመሳሰለ መለያ ምልክት (ታግ) በማዘጋጀት፣ የዘር መያዣ ከረጢት አመሳስሎ በማሳተም፣ የጥራት ቁጥጥር ያልተደረገበትን በተለይም በአርሶ አደሩ ዘንድ በስፋት የሚፈለጉና የአቅርቦት እጥረት ያለባቸውን ዝርያዎች በህገ-ወጥ መንገድ በመሸጥ አርሶ አደሩን ለከፍተኛ ኪሳራ ለመዳረግ ጥረት ማድረግ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም መላው አርሶ አደርና ሌሎች ዘርና የግብርና ግብዓት ተጠቃሚዎች ከእንደነዚህ ዓይነት ህገ ወጥ ዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓት አዘዋዋሪዎች ራስን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል ኃላፊው፡፡

በዚህም ዘር ለማከፋፈልና ለመቸርቸር ህጋዊ ብቃት ማረጋገጫ ካላቸውና በወረዳ ግብርና ጽ/ቤት በኩል ዘር እንዲሸጡ ህጋዊ ውክልና ከተሰጣቸው አካላት ብቻ መግዛት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ባለስልጣኑ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል ከዚህ በፊት ይጠቀምበት የነበረውን የዘር መለያ ምልክት ወደ ባርኮድ ህትመት መቀየሩንም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.