ለውጡ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በከፍተኛ እምርታ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እንዲደርስ አድርጓል – አምባሳደር ስለሺ በቀለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የለውጡ መንግሥት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የነበሩበት ተግዳሮቶች ላይ ማስተካከያ በማድረግ ግንባታው በከፍተኛ እምርታ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እንዲሻገር ማድረጉን አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የግድቡ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ፤ በግንባታው ሂደት ካጋጠሙ መሰናክሎች የፕሮጀክት አስተዳደር ላይ የነበሩ መሰረታዊ ችግሮች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
የፕሮጀክት አስተዳደር ሥራው ለሀገር ውስጥ ተቋራጭ የተሰጠበት መንገድ ትክክለኛ አካሄድን ያልተከተለና ውስብስብ መሆኑ የግድቡ ሥራ የሚፈልገውን የካበተ ልምድና እውቀት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደነበር አስታውሰዋል።
በወቅቱ የኮንክሪት ግንባታው በፍጥነትና በተያዘለት ጊዜ ቢከናወንም የኤሌክትሮ መካኒካልና ብረታ ብረት ሥራው በመጓተቱ የግድቡ ግንባታ እንዳይሳካ ፈተና እንደነበር ጠቅሰው፤ መንግስት ባደረገው የማስተካከያና የማሻሻያ ሥራ የግድቡ ግንባታ ሊፋጠን መቻሉን ተናግረዋል።
ሕዝቡ በራስ አቅም ግድቡን ለመገንባት ያሳየው ቁርጠኝነት ለግንባታው መፋጠን ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጉን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የግድቡ አጠቃላይ አፈጻጸም ትልቅ እምርታ አሳይቶ ከ95 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸዋል።
በተያዘው ዓመት መጨረሻ ድረስ የኮንክሪት ሥራው እንደሚጠናቀቅና አምስት ተጨማሪ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች እስከ ታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም ደረጃ በደረጃ ወደ ሥራ እንደሚገቡ አብራርተዋል።
የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን የኃይል አቅም በ130 በመቶ እንደሚያሳድግም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡