ለበልግ ወቅት የሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ መቅረቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለበልግ እርሻ ልማት 469 ሺህ 80 ነጥብ 84 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ ሙሉ በሙሉ ማቅረብ መቻሉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ለ2016/17 የምርት ዘመን 19 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚገዛና ከዚህ ውስጥ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ዩሪያ 11 ነጥብ 19 ሚሊየን ደግሞ ኤን ፒ ኤስ ማዳበሪያ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
የ2016/17 ምርት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ሥርጭት የእስከ አሁን አፈጻጸም ጥሩ መሆኑን ጠቁሞ÷ በአቅርቦት ደረጃ 1 ሚሊየን 678 ሺህ 730 ቶን ግዥ ተፈጽሟል ብሏል፡፡
ካለፈው ዓመት የከረመውን 56 ሺህ 193 ነጥብ 96 ሜትሪክ ቶን ጨምሮ ለምርት ዘመኑ ጥቅም ላይ ለማዋል በአዝመራ ወቅቶች ተለይቶ መታቀዱንም ጠቁሟል፡፡
በዚሁ መሰረት ለበጋ መስኖ ልማት 390 ሺህ 160 ሜትሪክ ቶን ለማቅረብ ታቅዶ ሙሉ በሙሉ ማቅረብ መቻሉን እና 66 ሺህ 497 ነጥብ 65 ሜትሪክ ቶን ለተጠቃሚው መሠራጨቱን ነው የገለጸው፡፡
እንዲሁም ለበልግ እርሻ ልማት 469 ሺህ 80 ነጥብ 84 ሜትሪክ ቶን ለማቅረብ ታቅዶ ሙሉ በሙሉ ማቅረብ መቻሉን በመግለጽ÷ 141 ሺህ 964 ነጥብ 21 ሜትሪክ ቶን ለተጠቃሚው መሠራጨቱን አመላክቷል፡፡
ለመስኖ እና ለበልግ እርሻ ልማት በድምሩ 208 ሺህ 461 ነጥብ 86 ሜትሪክ ቶን ለተጠቃሚው መሠራጨቱንም ነው ያስታወቀው፡፡
በአጠቃላይ የእስከ አሁን የአቅርቦትና ሥርጭት አፈጻጸም ሲታይም በድምሩ 1 ሚሊየን 65 ሺህ 997 ነጥብ 97 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ መድረሱንም ጠቅሷል፡፡
እስከ መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜም 973 ሺህ 774 ነጥብ 40 ሜትሪክ ቶን ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
በዚህ መሰረት የከረመውን ጨምሮ እስከ አሁን 1 ሚሊየን 29 ሺህ 968 ነጥብ 36 ሜትሪክ ቶን ቀርቦ ሥርጭቱ ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡