Fana: At a Speed of Life!

በሰብአዊ መብት ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት መንግስት በዘርፉ ለሚያከናውነው ስራ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰብአዊ መብት ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት መንግስት በዘርፉ ለሚያከናውነው ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተጠቆመ።

71ኛው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን “ወጣትነት ለሰላምና ሰብአዊ መብቶች መከበር” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለን ጨምሮ በርካታ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ተሳትፈዋል።

በአከባበር ስነ ስርአቱ ላይ በሰላምና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይም በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሲስተዋሉ በነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርገዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ፥ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በመንግስት በኩል በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ እንደነበረ በማስታወስ፤ አሁን ላይ እየተቀረፉ ነው ብለዋል።

ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ አክለውም፥ ከዚህ ቀደም የሰብአዊ መብት ጥሰት ችግሮች በመንግስት በኩል ነበሩ፤ አሁን ላይ ግለሰቦች እና ቡድኖች የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፅሙ እንደሚስተዋልም አስታውቅዋል።

ይህንን ለማስቆም መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ አለብን ያሉ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቶችም በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ አይደራደሩም ብለዋል።

አሁን የሰብአዊ መብትን ጥሰትን ለመከላከል የተፈጠረንው እንድል ተጠቅሞ እስከ መጨረሻ መጓዝ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል የህግ ማሻሻያዎችን ጨምሮ አዋጅ መጽደቁ የተገለፀ ሲሆን፥ ይህም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ምልእክት ተላልፏል።

አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን፤ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ሰነድ የወጣበት ቀንን ምክንያት በማድረግ ነው በዓሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ህዳር 30 ቀን የሚከበረው።

በሀይለኢየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.