የሀገር ውስጥ ዜና

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተጣብቀው የተወለዱ መንትዮችን በቀዶ ሕክምና እንዲለያዩ አደረገ

By Melaku Gedif

April 03, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተጣብቀው የተወለዱ መንትዮችን በቀዶ ሕክምና በተሳካ ሁኔታ እንዲለያዩ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ቀዶ ሕክምናውን የሰሩት በሆስፒታሉ የህጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ሙሉዓለም አማረ÷ ”ሞኖዚጎቲክ” መንትዮች የሚፈጠሩት ከአንድ ቀደምት ጽንስ ክፍፍል እና መለያየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መሰል ክስተት ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ከሚወለዱ ሕጻናት መካከል አንዱ ሊያጋጥም እንደሚችል መላምቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባጋጠመው ተመሳሳይ የሆነ የአፈጣጠር ችግር ምክንያት የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ችግሩ መቀረፉን አንስተዋል፡፡

አንደኛው ህጻን በሕይወት የተወለደ ሲሆን÷ ህጻኑ በተወለደ በአምስተኛ ቀኑ በተደረገ ቀዶ ሕክምና ከህጻኑ ጋር ተጣብቆ የተወለደውንና በሕይወት ከሌለው መንትያ ጋር በተሳካ ሁኔታ መለየት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በሕይወት የተረፈው ህጻን በሰላም ወደ ቤቱ መመለሱን ጠቁመው÷ የህጻኑን ጤንነት በቅርበት መከታተል ይቻል ዘንድ ሁኔታዎች እንደተመቻቹ መናገራቸውንም የሆስፒታሉ መረጃ ያመላክታል፡፡