Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካፒታል አሰባሰበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካፒታል በማሰባሰብ ከዕቅዱ በላይ ማሳካት መቻሉን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ የካፒታል ማሰባሰብ ሂደቱን ማጠናቀቁንም ዛሬ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

ተቋሙ በአዲስ አበባ፣ ናይሮቢ እና ለንደን በተደረጉ ባለሀብቶችን የማግባባት እና የማሳመን ስራ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉን ገልጿል።

ገበያው 631 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉም ነው የተገለፀው፡፡

ይህም ከእቅዱ በላይ 240 በመቶ ማሳካት እንዳስቻለው ነው የገበያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ያነሱት።

የሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያው በግል እና በመንግስት አጋርነት የተቋቋመ ሲሆን÷ መንግስት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል የ25 በመቶ የተፈቀደ ካፒታል ድርሻ ሲይዝ የግል ዘርፉ ደግሞ 75 በመቶ ድርሻ ይዟል ነው የተባለው።

በተጨማሪም የሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያው በመጪዎቹ ወራት ወደ ስራ ለማስገባት ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ እና ዋና ዋና ስራዎቹን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ነው ገበያው በዛሬው መግለጫው ላይ ያመለከተው።

በተጨማሪም የገበያው ሕገ ደንብ ህዝብ አስተያየት እንዲሰጥበት ይፋ መደረጉንም ነው ያነሱት፡፡

በአሸናፊ ሽብሩ፣ ህይወት አበበ እና ፍቅርተ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.