በ2ኛ ዙር ወደ ሀገር ለሚገቡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አቀባበል እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁለተኛ ዙር ወደ ሀገር ለሚገቡ በውጭ ለሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል እየተደረገ ነው፡፡
በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የተደረገውን ጥሪ መሰረት በማድረግ ቀጣይ በዓላትን ለማክበር እና የዕረፍት ጊዜያቸውን በሀገራቸው ለማሳለፍ በርካታ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን መግባታቸውን አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ተናግረዋል።
እስከ ሚያዚያ በሚቀጥለው በሁለተኛ ዙር ወደ ሀገር ለሚገቡ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያ የተለያዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ኢትዮጵያውያኑ በሀገራቸው ጥሩ ጊዜን እንዲያሳልፉ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
“ባክ ቱ ዩር ኦሪጅንስ“የሚል ስያሜ የተሰጠው እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጭ ለሚኖሩ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡት ጥሪ በሶስት ዙሮች የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዚህም ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በመጀመሪያው ዙር “ከብዝኃ ባህል መሰረትዎ ጋር ይገናኙ” በሚል መሪ ሃሳብ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መግባታቸው ይታወሳል።
አሁን ደግሞ ታሪካዊ “መሰረትዎን ይወቁ ” በሚል በተሰየመው መርሐ ግብር በሁለተኛ ዙር ወደ ሀገር እየገቡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
በቅድስት አባተ