የፊቼ ጨምበላላ ዋዜማ በሐዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊቼ ጨምበላላ ዋዜማ ዛሬ በሐዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡
በነገው ዕለት የፊቼ ጨምባላላ በዓል በርካቶች በተገኙበት በአደባባይ የሚከበር ሲሆን÷ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምታትም በየአካባቢው በዓሉ እየተከበረ እንደሚቆይ ተመላክቷል፡፡
ዛሬ ከምሽቱ 12 ሠዓት ጀምሮ አያንቶዎች፣ ጪሜሳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በየአካባቢያቸው ጾም እንደሚፈቱ ተገልጿል፡፡
በአብሮነት በሚያልፈው የዛሬ ምሽት ሥርዓት ላይ አብሮ መመገብ ይኖራል ፤ ልጃገረዶችም ሆሬ የተሰኘውን ባህላዊ ጫወታዎችን ይጫወታሉ፡፡
በዓሉ ወደ አዲስ ዓመት መሻገሪያ በመሆኑ የሁሉቃ ሥርዓት የሚፈጸም ይሆናል፡፡
በዓለም የትምህርት፣ ሣይንስ እና ባህል ድርጅት በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው ፊቼ ጨምባላላ÷ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ አንድነትና አብሮነት የሚንፀባረቅበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በብርሃኑ በጋሻውና አፈወርቅ እያዩ