የዓድዋ ድል ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ሰራዊቱን የሚጠቅም ባለራዕይ ተቋም ነው – ሌ/ጀ ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በኢኮኖሚው መስክ ወደፊት ሰራዊቱን የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ ባለራዕይ ተቋም ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ፡፡
አየር ኃይሉ በሰራዊቱ ስም ተቋቁሞ በቅርቡ ወደ ስራ ከገባው የዓድዋ ድል ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የ10 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ግዢ ፈፅሟል።
በአክሲዮን ግዢው ስነ ስርዓት ላይ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ÷ የዓድዋ ድል ማይክሮ ፋይናንስ በተቋማዊ ሪፎርሙ የሰራዊቱን አሰፋፈር እና አኗኗሩን ማዕከል አድርጎ የተቋቋመ የፋይናንስ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ የሰራዊቱን የቁጠባ ባህል ከማሳደጉም ባለፈ ብድር በማመቻቸት ሰራዊቱ ደረጃ በደረጃ ኑሮው የሚሻሻልበትን ሁኔታ ዘርግቶ የሚሰራ ባለራዕይ ተቋም መሆኑን አስገንዝበዋል።
አየር ኃይሉ ከተቋሙ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ሰራዊቱ በግል እየገዛቸው ካሉ አክሲዮኖች በተጨማሪ እንደ ተቋም የ10 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ግዢ ማከናወኑን ገልፀው፤ በቀጣይም አክሲዮኑን ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የዓድዋ ድል ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄኔራል ደረጄ መገርሳ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደ ተቋም ለፈፀመው የአክሲዮን ግዢ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሌሎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት ክፍሎችም አየር ሀይልን ምሳሌ በማድረግ ከተቋሙ ጋር የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡