Fana: At a Speed of Life!

190 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው፤ የ5 ሰዎች ህይወት አልፏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4 ሺህ 599 የላብራቶሪ ምርመራ 190 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 336 መድረሱንም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ ባወጡት ሪፖርት አመላክተዋል።

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ እድሜያቸው ከ1 እስከ 89 ዓመት የሆኑ 135 ወንዶችና 55 ሴቶች ናቸው።

ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 153 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፥ 16 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣10 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 3 ሰዎች ከሐረሪ ክልል፣ 3 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 3 ሰዎች ከደቡብ ክልል እንዲሁም 2 ሰዎች ከትግራይ ክልል ናቸው።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ የአምስት ኢትዮጵያውያን ህይወት ማለፉንም ዶክተር ሊያ በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

ህይወታቸው ያለፈው አምስቱም ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ እድሜያቸው 42 እና 40 ዓመት ወንዶች በህክምና ማእከል ህክምና ላይ የነበሩ እንዲሁም የ85 ዓመት እድሜ ያላቸው ሴት በጤኗ ተቋም ህክምና ላይ የነበሩ ሲሆኑ፥ እድሜያቸው 32 ዓመት የሆነ ሴት እና 40 ዓመት የሆነ ወንድ በአስክሬናቸው ላይ በተደረገ ምርመራ ቫይረሱ የተገኘ መሆኑን ገልፀዋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 32 መድረሱን በመጥቀስ፤ በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ፤ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት አስራ 18 ሰዎች (11 ከአዲስ አበባ፣ 5 ከአማራ ክልል እና 2 ከሶማሌ ክልል) ያገገሙ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 379 መድረሱንም አስታውቀዋል።

በትላንትናው ዕለት ሪፖርት በተደረገው የዕለታዊ መግለጫ ቫይረሱ በምርመራ እንድተገኘባቸው ከተገለፁት ሰዎች 10 ሰዎች ከዚህ ቀደም ሪፖርት ተደርገው በህክምና ማዕከል ውስጥ ያሉ እና ለክትትል ምርመራ የተደረገላቸው መሆናቸውን ከይቅርታ ጋር እንገልፃለን ብለዋል።

በመሆኑም በትላንትናው ዕለት ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር አንድ መቶ ሃያ ስድስት 126 መሆናቸውንም ባወጡት ማስተካከያ አብራርተዋል።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ152 ሺህ 334 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 336 ደርሷል።

አሁን ላይ 1 ሺህ 923 ሰዎች በህክምና ላይ ሲሆኑ፥ ከእነዚህም ውስጥ 32 ሰዎች በጽኑ የታመሙ መሆናቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

እስካሁን በኢትዮጵያ 379 ሰዎች ከቫይረሱ ሲያገገሙ፤ የ32 ሰዎች ህይወት አልፏል፤ 2 ሰዎች ወደ ሀገራቸው ጃፓን መመለሳቸው ይታወሳል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.