የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

By Mikias Ayele

April 08, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ከኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀንኬ ብርነስ ሰዋት ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እና ትብብር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መክረዋል፡፡

አምባሳደር ታዬ፥ የኔዘርላንድስ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር በልማት፣ በኢንቨስትመንትና በሰብዓዊ እርዳታ መስክ ያለውን ትብብር አድንቀዋል።

ተጨማሪ ትብብሮችን ለማጎልበት በሚያስችሉ የኢኮኖሚ መስኮች አብሮ መስራት እንደሚገባ መግለጻቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡

ሀንኬ ብርነስ ሰዋት በበኩላቸው÷ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጠንካራና ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል እንደምትፈልግ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ከ100 በላይ የኔዘርላንድስ ኩንባንያዎች በኢንቨስትመንት መሰመራታቸውን ጠቁመው÷በንግድና ኢንቨስትመንት የበለጠ ለመተባበር የሀገራቸው ፍላጎት መሆኑን አንስተዋል።

ሚኒስትሮቹ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮ ለመስራት መምከራቸውም ተጠቁሟል፡፡