ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በመተዛዘንና መረዳዳት እንዲሆን ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማብላት፣ በማጠጣት፣ በመተዛዘንና መረዳዳት እንዲሆን የሐረሪ ክልል መንግሥት ጥሪ አቀረበ፡፡
የክልሉ መንግሥት ለ1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም÷ ሕዝበ ሙስሊሙ በተለይም በረመዳን ፆም ወቅት ያሳየውን የመደጋገፍና መረዳዳት እሴቶችን በማጠናከር እንዲሁም ሰላምንና አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ በዓሉን እንዲያከብር ጠይቋል፡፡
መላው የክልሉ ሕዝብም በክልሉ ሰላምን፣ አብሮነትን፣ መተባበርንና ወንድማማችነትን በማጠናከር በክልሉ እየተከናወኑ በሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ላይ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ ቀርቧል፡፡
በዓሉም የሰላም፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆንም የክልሉ መንግሥት መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡