ከ304 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ304 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ዕቃዎቹ የተያዙት የጉምሩክ ኮሚሽን ከመጋቢት 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል እንደሆነ ገልጿል፡፡
በዚህም 251 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 53 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የወጭ፤ በድምሩ 304 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸው ተመላክቷል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይት፣ የቁም እንስሳት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ሞያሌ፣ ሐዋሳና ኮምቦልቻ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል።
በቅደም ተከተላቸውም 85 ሚሊየን፣ 64 ሚሊየን እና 47 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዛቸው ተገልጿል።
ኮንትሮባንዱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 18 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ እንደተያዙም ገልጾ አመስግኗል፡፡