የሀገር ውስጥ ዜና

በዶ/ር መቅደስ ዳባ የተመራ ልዑክ አይደር ሪፈራል ሆስፒታልን ጎበኘ

By Melaku Gedif

April 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የተመራ ልዑክ በመቀሌ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል እና የአፎሚ ሜዲካል ግላቭ ማምረቻ ማዕከልን ጎበኘ፡፡

ልዑካኑ በጉብኝታቸው በአይደር ሪፈራል ሆስፒታል በመገንባት ላይ የሚገኘውን የካንሰር ጨረራ ሕክምና መስጫ ማዕከል ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡

እንዲሁም በአይደር ሆስፒታል እየተሰጡ የሚገኙ የሕክምና አገልግሎቶችን መመልከታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ጠቁሟል፡፡

አፎሚ ሜዲካል ግላቭ ማምረቻ ማዕከል በሰዓት 4 ሺህ 500 ጥንድ እና 9 ሺህ ነጠላ ግላቮችን በማምረት ላይ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

አምራች እና ጤናማ ዜጋ ከመፍጠር አንጻር በተለይ የሀገር ውስጥ ምርትን በመጠቀም የውጪ ምንዛሬ በማስቀረት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር መቅደስ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ የሰርጂካል ግላቭንም ወደ ማምረት እንዲገባ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ልዑካኑ የቤን መስከረም ጠቅላላ ሆስፒታልንም የጎበኙ ሲሆን÷ በዚህም በሆስፒታሉ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብርን ለማጠናከር አበረታች ሥራዎች እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የክትባት እና የጂን ኤክስፐርት ማሽን ድጋፍ ለሆስፒታሉ እንደተደረገለት የሆስፒታሉ የሥራ ሃላፊዎች በጉብኝቱ ወቅት አንስተዋል።