ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ የዲጂታል የትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ምክር ቤቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ እና ስራዎቹን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው ሪፖርት ያደርጋል።
ምክር ቤቱ ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋት አስፈላጊ ስራዎችን በመለየት የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ምክረ ሃሳብ በማቅረብ እና የወጡ ፖሊሲዎች ውጤታማነትን የሚገመግም መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ የዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተፈፃሚነታቸውን በየጊዜው መከታተል አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምክር ቤቱ ይህንን ታሳቢ በማድረግ መደራጀቱን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የወጡ ፖሊሲዎች በውጤታማነት እንዲተገበሩ የመከታተል ተግባራትንም እንደሚያከናውን ጨምረው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው÷ ምክር ቤቱ ቅንጅታው አሰራርን በማጎልበት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ዕቅዶች እንድታሳካ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እውን እንዲሆን የተጀመሩ ተግባራትን የበለጠ ማጠናከር ላይ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ናቸው፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው ቀደም ብሎ ተቋቁሞ በነበረው ግብረ ሃይል የተሰሩ ስራዎችን ሂደት መመልከቱን ገልጸው፤ በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ አቅጣጫ ማስቀመጡንም አመልክተዋል።