ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በባዝል ከተማ ተወያይተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በስዊዘርላንድ 3ኛው የዓለም ዓቀፍ የትብብር መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን÷ ከዚህ ጎን ለጎንም በስዊዘርላንድ ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ጋር መክረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ በዚሁ ወቅት÷ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ማጠናከርና ተሳትፏቸውንም ማሳደግ እንደሚገባቸው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያውያን የሰላምን ዋጋ መረዳትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር እንደሚኖርባቸው ገልጸው፤ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ የዳያስፖራ አባላት በበኩላቸው÷ ከፕሬዝዳንቷ ጋር የሚወያዩበት መድረክ በመመቻቸቱ አመስግነው፤ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው የሰላም እጦት እንደሚያሳስባቸው በመጥቀስ፤ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ መግለጻቸውን በጄኔቫ ከኢፌዴሪ ቋሚ ተጠሪ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጠሪ ጽ/ቤቱም ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራትና የዳያስፖራውን ሁለገብ ተሳትፎ ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በጄኔቫ የኢፌዴሪ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ጸጋአብ ከበበው አረጋግጠዋል።