ያዲያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አምራች ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልግ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤሌክትሪክ የተለያዩ ዓይነት የሁለት እግር ተሽከርካሪዎችና ስኩተሮች አምራች ያዲያ ዓለም አቀፍ የቻይና ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልግ ገለጸ።
የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ዘመን ጁነዲን የኩባንያውን ዋና ስራ አስኪያጅና ከፍተኛ ኃላፊዎች ተቀብለው አነጋግረዋል።
የኩባንያው ኃላፊዎች ስለ ኩባንያው፣ ስለ ኢንቨስትመንት እቅዱ እንዲሁም ኩባንያው ያለበትን ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡
በፓርኮች ስላሉ መሰረተ-ልማቶች፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ማበረታቻዎችን የተመለከቱ ተያያዥ የኢንቨስትመንት ጉዳዮች ጭምር ውይይት ተደርጎባቸዋል።
አቶ ዘመን አክለው እንዳሉት ፥ ኩባንያው የተሰማራበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደ ሀገር ባለፉት አምስት ዓመታት እየተተገበረ ካለውና በአጭር ጊዜ ውጤታማ ከሆነው የአረንጓዴ ልማት ስራ ጋር ተመጋጋቢ ነው፡፡
ለኢንቨስትመንቱ መሳካት ኮርፖሬሽኑ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት።
መቀመጫውን ቻይና ያደረገው ያዲያ ኩባኒያ በፈረንጆቹ 2001 የተመሰረተ የተለያዩ ባለ ሁለት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል፡፡
ምርቶቹን ከመቶ በላይ ሀገራት የሚያቀርብ፣ በሽያጭ መጠን ላለፉት 6 ዓመታት ቁጥር አንድ የሆነና አረንጓዴ ከባቢን የሚያበረታታ ግዙፍ አምራች ኩባንያ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡