የሰንበት ገበያን በማስፋት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተጀመሩ አበረታች ሥራዎች ይጠናከራሉ-አቶ ገብረመስቀል ጫላ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰንበት ገበያን በማስፋት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተጀመሩ አበረታች ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች በወላይታ ሶዶ ከተማ በገበያ ማረጋጋትና በሌማት ትሩፋት መርሀግብር የተከናወኑ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በዚህ ጊዜ ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል እንደገለጹት÷ በየአካባቢው የሰንበት ገበያን በማቋቋም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሰራ ነው።
የሰንበት ገበያ ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እድል በመፍጠሩ በዘርፉ የተጀመሩ አበረታች ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
መንግስት በሰንበት ገበያ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ ከማገናኘት ባለፈ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን ወስዶ ውጤታማ ሥራ እየሰራ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሚኒስትሩ ሰሞኑን በሻሸመኔ፣ በሀዋሳ፣ በአርባ ምንጭ እና በወላይታ ሶዶ ከተሞች ባደረጓቸው ጉብኝቶች በሰንበት ገበያ፣ በሌማት ትሩፋትና ሌሎች የልማት ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን መመልከታቸውንም ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ እነዚህን ተግባራት በሁሉም አካባቢዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።