የሀገር ውስጥ ዜና

የአፋር ክልል የዳያስፖራውን አቅም በላቀ ደረጃ ለመጠቀም እንደሚሰራ አስታወቀ

By Meseret Awoke

April 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል የዳያስፖራውን አቅም በላቀ ደረጃ ለመጠቀም ይሰራል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አቅምና ፍላጎትን ማሰተናገድ የሚያስችሉ የዳያስፖራ ተሳትፎ ጥቅሎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመለየትና ለመቅረጽ በክልሎችና ከተማ አስተዳደድሮች በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተካሄደው ውይይት አቶ አወል አርባ፥ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ዳያስፖራው እያደረገ ባለው ተሳትፎ ለሀገራችን የልማት አጋዥ ኃይል ነው ብለዋል፡፡

ይህንን አቅም በላቀ ደረጃ ለመጠቀም እንደ ክልል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው፥ ክልሉ የዳያስፖራ ተሳትፎን የሚያጎለብቱ ጥቅሎችን ለማዘጋጀት ያለውን ቁርጠኝነትና ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

ዳያስፖራው አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን በማውገዝ አዎንታዊ ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የክልሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ሀመዱ ጋአስ በበኩላቸው፥ ክልሉ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው 100 የኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ 33ቱ ለዳያስፖራ ብቻ መለየታቸውን አንስተዋል፡፡

በተናጠልም ሆነ በተደራጀ ሁኔታ በክልሉ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉ ዳያስፖራዎችን በተለየ ሁኔታ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።

በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተዘጋጀው የዳያስፖራ ተሳትፎ ጥቅል ቀረጻ ጠቋሚ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የዳያስፖራን ተሳትፎን ከማሳደግ ጋር በተያያዘም ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የክልሉ ቢሮዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ከዳያስፖራ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።