ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ልትጥል ነው

By Mikias Ayele

April 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደምትጥል አስታወቀች፡፡

የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን÷ አሜሪካ የኢራን ሰው አልባ ድሮን እና ሚሳኤል ፕሮግራምን ኢላማ ያደረገ ማዕቀብ ትጥላለች ብለዋል፡፡

በተጨማሪም አሜሪካ የኢራን አብዮታዊ ዘብ እና መከላከያ ሚኒስቴርን በሚደግፉ አካላት ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል አስጠንቅቀዋል።

ኢራን በእስራኤል ላይ የፈፀመችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ የአፀፋ ምላሽ ለመስጠት ፕሬዚዳንት ባይደን የአሜሪካ አጋር ከሆኑት የቡድን 7 አባል ሀገራት እየመከሩ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ የአየር መካለከያዎች እና የቅደመ ማስጠንቀቂያ ሰርዓቶችን መገንባቷን ጠቅሰው፤ ይህም የኢራን ሚሳኤሎች በመካከለኛው ምስራቅ ውጤታማ እንዳይሆኑ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከመከላከሉ በተጨማሪ በኢራን ላይ የሚጣሉት አዳዲስ ማዕቀቦች የኢራንን ወታደራዊ አቅም የሚያዳክሙና የጦር መሳሪያ አቅምን ለመቆጣጠር የሚረዱ ናቸው ማለታቸውን የተለያዩ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡