ስፓርት

በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ በሚገኘው የቦክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካና ከሞሪሽየስ ጋር ትጋጠማለች

By Mikias Ayele

April 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ በሚገኘው የማንዴላ አፍሪካን ቦክሲንግ ካፕ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን ቦክሰኞች በሁለቱም ፆታ ከደቡብ አፍሪካ እና ከሞሪሽየስ አቻቸው ጋር ይፋለማሉ፡፡

ምሽት 1 ሰዓት በደርባን ከተማ በሚደረገው ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቦክሰኞች የመጀመሪያ ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ያደርጋሉ፡፡

በወንዶች 57 ኪሎ ግራም አብዱሰላም አቡበከር ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር የሚገጥም ሲሆን በ60 ኪሎ ግራም ደግሞ አቡበከር ሰፋን ከሞሪሽየስ አቻው ጋር የሚጋጠም ይሆናል፡፡

በ67 ኪሎ ግራም ወንዶች ኤርሚያስ መስፍን ከደቡብ አፍሪካ ተጋጣሚው ጋር ይፋለማል፡፡

በሴቶች በ66 ኪሎግራም የመላ አፍሪካ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዋ ቤተል ወልዴ ከደቡብ አፍሪካ አቻዋ ጋር የምትፋለም መሆኑን ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡