የቻይና ዓለም አቀፍ የቋንቋ ቀን በአዲስ አበባ ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 5ኛው የቻይና ዓለም አቀፍ የቋንቋ ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል።
ቀኑ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በኩል የቻይና ቋንቋ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆኖ እውቅና የተሰጠበትን መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር፣ የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትና የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ቻይና የብዙ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ባለቤት በመሆኗ ቋንቋዋ የአለም አቀፍ ቋንቋ ሆኖ እውቅና ማግኘቱ አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል።
ኢትዮጵያ እና ቻይና የቀደመ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ ሀገራት መሆናቸውም የተገለፀ ሲሆን÷ ይህ ግንኙነታቸው ዛሬም ድረስ በብዙ መስኩ መቀጠሉ ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ የቻይና ቋንቋ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መሰጠት መጀመሩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የበዓሉ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የቻይና ባህልና ቋንቋ የሚያሳዩ ትርኢቶች ቀርበዋል።
በሃይማኖት ኢያሱ