Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢዋን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት፣ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት ዙሪያ መክረዋል፡፡

አቶ አደም ፋራህ÷የኢትዮ-ቻይና ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉንና የቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ አጋርነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣ አንስተዋል።

ከዚህ በፊት በሁለቱ ፓርቲዎች ስምምነት መሰረት በትምህርት፣ በስልጠና እንዲሁም በተሞክሮና ልምድ ልውውጥ አብሮ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት የልዑካን ቡድን ውጤታማ ቆይታ አድረጎ መመለሱም የዚህ ስምምነት አካል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ለልዑካን ቡድኑ ለተደረገው አቀባበልና ስኬታማ የቆይታ ጊዜ ያላቸውን ምስጋና መግለጻቸውንም የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቶች በመሰል የስልጠናና የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብሮች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልፅግና ፓርቲ ፍላጎቱ እንደሆነ አብራርተዋል።

አምባሳደር ዣዎ ዢዋን በበኩላቸው÷የብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እየሰራቸው ያሉ ውጤታማ ስራዎችን አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቻይና ጠንካራ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው÷ይህ ግንኙነት በፓርቲ ለፓርቲም ሆነ በመንግስታዊ ወዳጅነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.