በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትና የተቀራረበ ግንዛቤ እንዲይዙ ምሁራን የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አስገነዘበ።
ሚኒስቴሩ “ዘመኑን የዋጀ አርበኝነት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ያስጀመረ ሲሆን፤ በዕለቱ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተወካዮች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፤ ከዚህ ቀደም “አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ከ40 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት መካሔዱን አስታውሰዋል።
በመድረኮቹ የጋራ ማንነት፣ እሴት እና ሀገራዊ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ስኬታማ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ ኩነቱ በቀጣይ ለሚካሔዱ የንቅናቄ መድረኮች ትልቅ ግብአት የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
ምሁራን መሰል ሀሳቦችን በማውረድ፣ በማወያየት እና በማዳበር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትና የተቀራረበ ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል የላቀ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በሁሉም ዘርፍ ለሀገር ልማትና ብሔራዊ ጥቅም ታማኝ ሆኖ መስራት ከዜጎች የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ በተለይም ምሁራን በዚህ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙ ፎረሞችም ከፍ ያሉ ሀሳቦችን በማንሳት ውይይት በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።