የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ከ19 ሺህ በላይ የምርት ጥራት ፍተሻ አገልግሎት ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ባለፉት 9 ወራት የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ከ19 ሺህ በላይ የምርት ጥራት ፍተሻ አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ እንዳሉት÷ ድርጅቱ በዋናነት የጥራት ፍተሻ ላቦራቶሪ፣ የጥራት ሰርተፊኬሽን እና የኢንስፔክሽን አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
በዚህም ባለፉት 9 ወራት ከ1 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ከ19 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ምርቶች በላብራቶሪ የጥራት ፍተሻና የሰርተፊኬሽን አገልግሎት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
ጅቡቲ በሚገኘው የድርጅቱ ቅርንጫፍም ከ31 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ላይ የላቦራቶሪ ፍተሻ ማድረጉን ነው ያነሱት።
ድርጅቱ የጥራት ፍተሻ አገልግሎት ከሚሰጣቸው ዘርፎች መካከል የግብርና ግብዓቶች፣ የምግብና መጠጥ፣ መድሃኒት፣ ኬሚካልና ማዕድን፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ የኤሌክትሮኒክስ የቆዳና ጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እንደሚገኙበት ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ምርቶቹ በተቀመጠላቸው መስፈርት መሰረት ደረጃቸውን ጠብቀው መመረታቸው ተፈትሾ የማረጋገጫ ሰርተፊኬት የተሰጣቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።