Fana: At a Speed of Life!

ሰላም እንደ ዛፍ ችግኝ ነው፤ እንክብካቤ ይፈልጋል- ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ሰላም እንደ ዛፍ ችግኝ ነው፤ ችግኝን ተክሎ ለማሳደግ ለማሳደግ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰላምም ጥሩ ልብ እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል” አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በኖርዌይ ኦስሎ ዛሬ በተከናወነው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በሰላም ዙሪያ ንግግርና ገለፃ አድርገዋል።

በንግግራቸውም የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የነበረው የድንበር አለመግባባት በሰላም እንዲቋጭ ለሰሩት ስራ ለሰጣቸው እውቅና ምስጋናን አቅርበዋል።

ሽልማቱንም በሀገራቱ መካከል ሰላም እንዲመጣ ዋጋ በከፈሉ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስም እንዲሁም ለኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት ቁርጠኛ በነበሩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስም እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።

“ዛሬ እዚህ ቆሜ ስለ ሰላም የምናገረው የእድል ጉዳይ ሆኖ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነት ሲጀመር ወጣት ወታደር ነበርኩ፤ የጦርነትን አስከፊነትን በአውደ ውጊያ በአካል ተገኝቼ ተመልክቻለሁ ብለዋል።

ጦርነትን ያላዩ ነገር ግን የሚያወድሱት ሰዎች አሉ ያሉ ሲሆን፥ እነዚህ ሰዎች በጦር ሜዳ ያለውን ፍራቻ፣ እልቂት፣ ውድመት እና የልብ ስብራትን ስላላዩ ነው፤ አዛውንቶች፣ ወጣቶች፣ ህጻናት እና ሴቶች በጦርነት ሲሰቃዩ እና ሲሞቱ ተመልክቻለሁ ብለዋል።

በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እና ንጹሃን ዜጎች ህይወት ማለፉን በመጥቀስ፥ ጦርነቱ በርካታ ቀውሶችን አስከትሎ እንደነበረም አስታውስዋል።

በሀገራቱ መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት ሰላም ርቆ በመቆየቱም ቤተሰቦች መለያየታቸውን እና በርካታ ሰራዊት በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ መሽጎ መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

ከ18 ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንደተመረጡም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጦርነት ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መለያየት መቆም እንዳለበት መወሰናቸውንም ተናግረዋል።

በመለያየት ፈንታም ለዘመናት የሚዘልቅ የሰላም፣ የትብብር እና የመልካም ወዳጅነት ድልድይ መገንባት እንዳለበት በመወሰን፤ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቀረበው ጥያቄ መሰረት አሁን ላይ በሀገራቱ መካከል ሰላም መስፈን መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ሁለቱ ሀገራት ጠላቶች እንዳልሆኑ ይልቁንስ ድህነት የጋራ ጣላታቸው እንደሆነ አውቀን ለሁለቱ ሀገራት እና ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ብልጽግና መስራት መጀመራቸውንም ተናግረዋል።

አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል የዲፕሎማሲ፣ የትራንስፖርት፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን እና ሌሎች ግንኙነቶች ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል ያሉ ሲሆን፥ አሁን ትኩረታችን በጋራ መልማት ብቻ ነውም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በንግግራቸው አክለውም፥ ጦርነትን ለማስጀመር ጥቂት ጊዜ ይበቃል፤ ሰላምን ለማምጣት ግን መንደር፣ ህዝብ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

ለእኔ ሰላምን ማምጣት ዛፍን ተክሎ ከማሳገድ ጋር ይመሳሰልብኛል ያሉ ሲሆን፥ ዛፍን ተክሎ ለማሳደግ ውሃ እና መልካም አፈር እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰላምን ለማምጣትም ጠንካራ ተነሳሽነት፣ ታጋሽነት እና መልካም ልብን ይፈልጋል ሲሉም ገልፀዋል።

“ለሰብአዊነት ያለን ፍቅር ሲጨምር ዓለም ሰላምን ታውቃለች” ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በመድረኩ ላይም ስለ መደመር ያብራሩ ሲሆን፥ መደመር ሀገር በቀል ሀሳብና የጋራ ብልጽግና ላይ ያተኮረ ሀሳብ መሆኑንም ተናግረዋል።

“በመደመር ጽንሰ ሀሳብ ውስጥም እኛ እና እነሱ የሚል ነገር የለም፤ በመደመር ውስጥ እኛ እና እኛ ብቻ ነው ያለው” ሲሉም አስረድተዋል።

አያይዘውም በኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ግንባታ ዘርፍ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ ግለሰቦችን እና ጋዜጠኞችን ከእስር መፍታትን ጨምሮ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን በማስታወስ፤ በቅርቡ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እናካሄደለን ብለዋል።

ለሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች ባስተላለፉት መልእክትም ለሰላም፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት መረጋገጥ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ መሆኑ ላይ በሰጡት ማብራሪያም “በሰላም እንድታድር ጎረቤትህ ሰላም ይደር”የሚለውን አባባል በማንሳት የአንዱ ሰላም ለሌላው አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያለውን እንቅስቃሴ አስመልክተውም የዓለም ሀያላን ሀገራት በአካባቢው ጦራቸውን እያሰፈሩ መሆኑን በማንሳት አሸባሪዎች እና ፅንፈኞችም በስፍራው ለማንሰራራት የሚያደርጉትን ጥረት ጠቅሰዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የዓለም ሀያላን ሀገራት የጦር አውድማ እንዲሆን አንፈቅድም በማለት፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሰላም እና የለውጥ ቀጠና እንድትሆን ነው የምንፈልገው ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

በሙለታ መንገሻ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.