Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ለጤናው ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የማይበገር የጤና ሥርዓትን እውን ለማድረግ እና ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን በማሻሻል ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከኮሚሽኑ ልዑክ ጋር በትብብር በሚሠሩ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ውይይት፤ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የጤናውን ዘርፍ ለማጠናከር የሚበረታታ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ የማይበገር የጤና ሥርዓትን ለመገንባት፣ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከልና አስፈላጊውን የጤና ምላሽ ለመስጠትና ሥርዓተ-ጾታን በጤናው ዘርፍ ለማካተት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የአዕምሮ ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ፣ የጤና ባለሙያዎችን ለማሰልጠንና ለማብቃት እንዲሁም በግጭት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋምና በመገንባት ረገድ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ላይ ኅብረቱ እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በቀጣናው የላቀ የባዮ ሜዲካል ላብራቶሪን ከማስፋፋትና ከራስ አልፎ ለሌሎች ሀገራትም አቅም መሆን የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበው÷ ኅብረቱ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊ ሮበርቶ ሺሊሮ በበኩላቸው÷ ተቋማቸው ለበርካታ ዓመታት የጤናው ዘርፍ አጋር በመሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የማይበገር የጤና ሥርዓት እውን ለማድረግ እና ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን በማሻሻል ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

በኅብረቱ የሚደገፉ ፕሮጀክቶን በተሳለጠ መልኩ ለማከናወንና ለውጣቸውንም በቅርበት እየተከታተሉ ለመገምገም የሚያስችል ስልት መንደፍ እንደሚገባ መጠቆማቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

የግሉን የጤና ዘርፍ ከማብቃት እና ተሳታፊ ከማድረግ አኳያም ከሚኒስቴሩ ጋር በመተባበር በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ነው የገለጹት፡፡

በግጭት ምክንያት የወደሙ ተቋማትን መልሶ በመገንባት፣ ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል እና ሥርዓተ-ጾታን በማካተት ረገድ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን በማብቃትም በትኩረት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.