ቴክ

ቮይስ ኢንጂን- የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውጤት

By Shambel Mihret

April 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጽሁፍን ወደ ተንቀሳቃሽ ምስል የሚቀይረውን መተግበሪያ ጨምሮ የተለያዩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የሚታወቀው “ኦፕን ኤአይ” አዲስ ቴክኖሎጂን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡

“ቮይስ ኢንጂን” የተሰኘው ሞዴል ከተናጋሪዎች የ15 ሴኮንድ የድምጽ ናሙና እና ጽሁፍን በመጠቀም አዲስ ድምጽ መፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል።

የሚፈጠረው ድምጽ የሰው ልጆችን ተፈጥሯዊ የንግግር ለዛ፣ ድምጸት እንዲሁም የንግግር መዋቅር የጠበቀ መሆኑንም የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ቴክኖሎጂው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከጊዜ በኋላ የመናገር እክል ለገጠማቸው ሰዎች ከቀደመ ድምጻቸው ናሙና በመውሰድ የሚፈልጉትን ነገር በቀላሉ መናገር እንዲችሉ ያግዛልም ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም አንድን ይዘት በቀላሉ ወደ ብዙ ቋንቋዎች ለመተርጎም ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

በሙከራ ደረጃ ውጤታማ የሆነው ቴክኖሎጂው ከግላዊ መብቶችና የቴክኖሎጂው አጠቃቀም ጋር የተያያዙ መመሪያዎች እስካሁን ይፋ እንዳልተደረጉለትም ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በየጊዜው ማሻሻያዎች ሲደረጉበት የቆየው ቴክኖሎጂው የሰው ሰራሽ አስተውሎት በስፋት ጥቅም ላይ መዋልን ተከትሎ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመነቃቃት ላይ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡