የሀገር ውስጥ ዜና

መንግሥት ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሠራ ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

April 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍቢ ሲ) መንግሥት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከርና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ ለዘመናት ሥር ሰደው የቆዩና ያለመግባባት መነሻ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት በርካታ የሪፎርም እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

ፖለቲካዊ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ መንግሥት በፅኑ ይሰራል ያሉት ሚኒስትሩ፥ የተፈጸሙ በደሎችን በእርቅ በይቅርታ እና በፍትሕ ለመሻገርም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መጽደቁን አስታውቀዋል፡፡

በሀገራዊ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርም ሕዝብ በአጀንዳዎቹ ላይ ምክክር አድርጎ መፍትሔ የሚያቀርብበት ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መንግሥት ኢትዮጵያዊ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ልዩ ትኩረት መስጠቱን አንስተው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያን አንድነት ለማፅናትና የሕዝቦችን የዘመናት አብሮነት በጠንካራ መሰረት ለማዝለቅ አሰባሳቢ ትርክት ሚናው የላቀ መሆኑንም ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

ለዚህም መንግሥት በብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ የጋራ ትርክትን መገንባት ላይ በቁርጠኝነት እየሠራ ነው ብለዋል።

የጋራ ትርክቱ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ክብሯን ለማስጠበቅ እንዲሁም የሕዝቡን አንድነት ለማጎልበት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትም የመንግሥት መረጃዎች ሳይፋለሱ ወቅታቸውን ጠብቀው ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር እንዲሁም ኅብረተሰቡ ለልማት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ላይ እየሰራ ነውም ብለዋል።

የተዛቡ መረጃዎችን መመከት፣ ልዩነትን የሚያባብሱ አስተሳሰቦችን ማረቅ እና የኅብረተሰቡን የአብሮነት እሴት ለሚያጎለብቱ ሥራዎች ትኩረት መሠጠቱንም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ አሰባሳቢ ትርክትና ኅብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን በተቀናጀ መልኩ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡