Fana: At a Speed of Life!

ሐረርን ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐረርን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ተስማሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት በከተማው የሚስተዋለውን የፕላስቲክ ቆሻሻን መልሶ ለማልማት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከኪዩቢክ ኢትዮዽያ ፕላስቲክ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር ተፈራርመዋል።

ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ሐረርን ለነዋሪውና ለጎብኚው ምቹና ተስማሚ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል፡፡

በፕላስቲክ ተጽዕኖ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከልና በዘርፉም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱም በክልሉ ያለውን ውስን መሬት ከቆሻሻ በማዳን በአግባቡ ለልማት መጠቀም ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አሰፋ ቶልቻ ኩባንያው የሚያከናውነው ሥራ ደረቅ ቆሻሻ የሆነውን ፕላስቲክ ወደ ሀብት የሚቀይር መሆኑን አመላክተው÷ ይህም ሥነ-ምኅዳርን በመጠበቅና የሥራ ዕድል በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን ያጎለብታል ብለዋል።

የኪዩቢክ ኢትዮዽያ ፕላስቲክ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ቅዱስ ፍስሃ በበኩላቸው÷ ኩባንያው የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በመፍጨት ጡብ፣ ብሎኬት፣ ኮለንና ሌሎች ለግንባታ የሚያገለግሉ ቁሶችን እንደሚያመርት ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የአካባቢንና የከተሞችን ውበት በማስጠበቅ ለዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.