ዓለምአቀፋዊ ዜና

ግሪክ ከሰሃራ በርሃ በተነሳ አውሎ ንፋስ በአሸዋ መሸፈኗ ተነገረ

By Tamrat Bishaw

April 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ግሪክ ከሰሃራ በርሃ አሸዋ አዝሎ በተነሳ አውሎ ንፋስ በአሸዋ ብናኝ መሸፈኗ ተገለጸ፡፡

ከአፍሪካ በተነሳ ከፍተኛ አቧራ አዘል የአሸዋ አውሎ ንፋስ አቴንስ እና ሌሎች የግሪክ ከተሞች የተሸፈኑ ሲሆን፤ የሀገሪቱ ሰማይ ብርቱካናማ ቀለም ባለው ብናኝ መጋረዱ ተመላክቷል፡፡

የሀገሪቱ ሜቲዎሮሎጂ አገልግሎት፤ በአብዛኛው በሰሜን እና ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው የሰሃራ አቧራማ አውሎ ንፋስ በጭቃ ዝናብ ሊታጀብ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

አውሎ ንፋሱ ከፍ ካለው የፀደይ ሙቀት ጋር በመገጣጠም ተፅዕኖውን እያጠናከረ መምጣቱን የአካባቢው የአየር ሁኔታ መረጃዎች አስገንዝበዋል።

አሸዋ ዘል አውሎ ንፋሱ የመተንፈሻ አካላት የጤና እክል ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ባለስልጣናት ማስጠንቀቃቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ንፋሱ ከዛሬ ጀምሮ ቀለል ያለ የአቧራ መጠን በመያዝም አቅጣጫውን ወደ ሀገሪቱ ምዕራብ ዳርቻ ክፍል እንደሚያደርግም ይጠበቃል ተብሏል፡፡