የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ የታዩ ልምዶች ይበልጥ መጎልበት ይገባቸዋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ረገድ የታዩ ልምዶች ይበልጥ መጎልበት እንዳለባቸው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን አስታወቀ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን÷የኮርፖሬሽኑን ዋና መሥሪያ ቤት፣ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና የቤቶች ልማት ፕሮጀክቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል÷ተቋማቸውን ከችግር በማውጣት ትርፋማና ተወዳዳሪ ተቋም ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በሪፎርሙ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር፣ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የኮርፖሬሽኑን የማስፈፀም አቅም ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የቤቶችን የይዞታ ካርታ በማዘጋጀት፣ ለቤቶች መለያ ምልክት በመለጠፍ፣ ጂ.ፒ.ኤስ እና ወደ ጎግል ካርታ በማስገባት የኮርፖሬሽኑን የቤት አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻል መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለ28 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የቤቶች ግንባታ ከማስጀመርም ባለፈ የጥራት፣ ጊዜና የግንባታ ዋጋ ማሻሻል ተችሏልም ነው ያሉት፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር)÷የኮርፖሬሽኑ የቤት አስተዳደር ሥርዓት ለማሻሻል የተጀመረው የቤቶች የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ከቤቶች ልማት ጎን ለጎን በቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገነባው የብሎኬት እና የኮንክሪት ማምረቻ ፋብሪካ የዘርፉን ችግር ከመፍታት ባለፈ ለኢንዱስትሪው ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ በበኩላቸው÷ የኮርፖሬሽኑ የቤቶች ግንባታ እንደ ሀገር ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በግንባታ ሂደት የሚሳተፉ ባለቤቶች፣ አማካሪዎችና ተቋራጮች ጥምረት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑን ተናግረዋ፡፡
የሱፐርቪዥን ቡድኑ በተመረጡና ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች የሚያደርገው የመስክ ምልከታ እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቀጥል ኢዜአ ዘግቧል፡፡